በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና የመሬት መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ድረ-ገጽ በለጸገ

154

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና የመሬት መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ድረ-ገጽ በለጸገ።

ድረ-ገጹ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ አገሮች በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ ለመስጠትና የአካባቢ ጥበቃ ለማከናወን እገዛ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከቀጠናው የተፈጥሮ ሃብት ልማር ካርታ ስራ ማዕከል አርሲኤምአርዲ) ጋር በመተባበር የመረጃ ልውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ የተገኙት የቀጠናዊ የመሬት ሃብት ልማት ካርታ ስራ ማዕከል (አርሲኤምአርዲ) የሪሞት ሴንሲንግ ኦፊሰር አቶ ደገሎ ሰንዳቦ እንደገለጹት፤ ፖርታሉ የመሬት አጠቃላይ መረጃን በማቅረብ ለአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ድረ-ገጹ መረጃውን በመጫን በቀጠናው የመሬት ጥቅል መረጃ ተደራሽ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የተጎዱ የመሬት ክፍሎችን በመጠቆም መፍትሄ እንዲሰጣቸው ማድረግ የፖርታሉ አንደኛው አላማ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደገሎ፤ ረግረጋማ ስፍራዎች ጉዳት እያጋጠማቸው እንደሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች መሰባሰባቸውን ተናግረዋል።

የረግረጋማ ስፍራዎች እየደረቁ መምጣታቸው በአካባቢው ብዝሃ ህይወት ላይ አሉታዊ ጫና እያስከተለ እንደሚገኝምና የከርሰ ምድር ውሃ መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

መሬት ከተጎዳ በኋላ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ፈታኝ መሆኑን ገልጸው፤ ከወዲሁ የመከላከል ስራ መስራት ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ ስለ መሬት ሁኔታ መረጃ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የበለጸገው ድረ-ገጽ ለዚህ መፍትሄ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ድረ-ገጹ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለተመራማሪዎች የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል አቶ ደገሎ ጠቁመዋል።

የድረ-ገጹ አንዷ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ በበኩላቸው አገሪቱ የመሬት መራቆትን በተመለከተ ሰፊ ጥናት ማካሄዷን ገልጸዋል።

የተጠኑ ጥናቶች አሁን በበለጸገው ድረ-ገጽ ላይ ተጭነው የመሬት መረጃ ምንጭ ሆነው እንዲያገለግሉ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በማዕከሉ ውስጥ አስተዋጽኦ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ የተደራጀ የመሬት መረጃ እንደያዘች ነው የገለጹት።

መረጃዎቹ የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ፣ የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም እና መሬቱ ውሃ የሚያመነጭበትን አቅም ለማሳደግ ጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የመሬት መረጃ ለህዝብ ተደራሽ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ዶክተር ቱሉ፤ የድረ-ገጹ መበልጸግ በዚህ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የድረ-ገጹ ተጠቃሚዎች ተሳትፎ ጉዳይ ሃላፊ ኬኔት ካሴራ የሚጫኑ መረጃዎች የሚሰባሰቡት አስተማማኝ ምንጭ ከሆኑ የተለያዩ የቀጣናው አገሮች ተቋማት መሆኑን ተናግረዋል።

መረጃዎቹ የተጣሩና ከስህተት የጸዱ እንዲሆኑ ተገቢው ጥንቃቄ እንደሚደረግ ገልጸው፤ የመረጃዎቹ ምንጭ አብሮ እንደሚያያዝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም